በ 50ዎቹ ና በ 60ዎቹ ዘመናዊ ሙዚቃ፣ ፉሽን ና የምሽት ህይወት አዲስ አበባ ውስጥ በተለይ አራዳ አካባቢ ሲያብብ፥ ከዚያ ጋር ተያይዞ ስማቸው በዋናነት ይጠቀሱ ከነበሩት መካከል ሜሪ አርምዴ አንዷ ነበረች። በወቅቱ የገነነ ስም ቢኖራትም፥ ስለእርሷ የተፃፉ ብዙ መረጃ ማግኘት አዳጋች ነው።ይህንን እውነታ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ቀጣዩን መነን መፅሔት መጋቢት 1965 የታተመ ፅሑፍ እዚህ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ አትመንዋል።
እኔ መጀመሪያ አርቲስት ለመሆን የመረጥኩት ገና ትንሽ ልጅ ሆኜ ነው።የተወለድኩት አራዳ ጊዮርጊስ ነው። በሠፈራችን መደዳውን ጠጅ ቤት ነበር።ዘውትር ይዘፈናል። እኔም የታዘዝኩትን ትቼ ወደዚያው ሄጄ ቀስ ብየ እያሾለኩ በመጋረጃ ውስጥ እመለከታለሁ።የዚያን ጊዜ ዘፋኞቹ እነ ባፈና ወልዱ፥ ንጋቷ ከልካይ፥ እነ ጥሩ ብርቄ ነበሩ።እነሱኑ በመመልከት ስሜት ያዘኛና አንጐራጉር ጀመር።ሰውም “ነይ እስቲ ሜሪማ ዝፈኝልን” ይለኛል።ያኔ ስሜ ሜሪማ ነበር። የአራዳ ሴቶች መሪ ከሆንኩኝ በኅላ ስሜን ሜሪ ብየ ቀየርኩት።አባቴ ጐንደሬ እናቴ ራያ ናቸው።እነሱ ናቸው ሜሪማ ብለው ስም ያወጡልኝ።
ይኄውልህ አርቲስት ለመሆን የነበረኝ ስሜት ከዚያን ጊዜ ነው የጀመረው።በጠላት ጊዜ እንኳ ምንም ልጅ ብሆን፥ ይባል የነበረውን ሁሉ አንጐራጉር ነበር።
ሜሪ አርሚዴ ፋቄ የሚባል ሀገር ሁለት ዓመት በስደት ኖራለች። በኃላም የፋሽስት መንግስት “መንኩሴዎች ፥ህፃናት፥ደካሞች ተመለሱ” ብሎ ሲያውጅ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰችና እዚያው ቀድሞ ሠፈሯ አራዳ ገባች።ሜሪ ስትናገር “ዘመዶቼ ሙያ እንዳውቅ በይ ፍተይ፥ ስፌት ስፊ” ሲሉኝ አሻፈረኝ እያልኩ ማንጐራር ብቻ ሆነ።ነጋ ጠባ እገረፋለሁ።እኔ ግን አንዴ በዚህ ተለክፌያለሁና ውሎየ ጠጅ ቤት ሆነ።ቤተዘመድ ተሰብስቦ መከረና ሚሲዮኖች ዘንድ ሄጄ እንድማር ተደረገ።እዚያም ሄጄ ትምህርቱ አልሆነልኝም።ማንጐራር ሆነና መምህራኑን አስቆጣቸው።በኃላም ይህቺ ልጅ ዘፈን እንጂ ትምህርት አይሆናትም፥ ደህና ልጆችን መጥፎ ትምህርት ታስተምርብናለች ብለው ትምህርት ቤቱን እንድለቅ አደረጉ። ዘመዶቼም ተናደው እንደገና እዚያው ትምህርት ቤት አንጠልጥለው ወሰዱኝና ጫጩትም ቢሆን እዚሁ ትምህርት ቤት ሆና ትጠብቅ እንጂ እቤት ውላ ጠባይዋ ሊሻሻል አይችልም ብለው የትምህርት ቤቱን አስተዳዳሪ ለመኗቸው።እርሳቸውም የቤተሰቦቼን መጨነቅ አይተው ለሁለተኛ ጊዜ ተቀበሉኝ። ሜሪማ እንደሆንኩ አሁንም ሀሳቤ እዚያው ጠጅ ቤት ነኝ።ጓደኞቼ ከመፅሐፍ ጋር ሲታገሉ እኔ አንጕራጉራለሁ። የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪ የነበሩት መነኩሴ ተበሳጭተው ሁለተኛ ዓይኗን እንዳላይ ብለው አባረሩኝ።የትምህርቴም ነገር በዚሁ አከተመ።
አራዳ ጊዮርጊስ ከሚገኙት ጠጅ ቤቶች ከሚገኙትጐራ እያልኩ መዝፈኔን ቀጠልኩ።ከጊዜ በኅላ ከአንዲት ፈረንሳዊት ጋር ተዋወቅሁ።ከእርሷም ጋር ፍቅራችን የጠና ሆነ።በዘመኑ ብርቅ የነበሩትን ዳንሶች አጠናሁ። በዚሁ ሙያዩ ሰው ሁሉ ጉድ አለ።ያን ጊዜ በውስጥ ሱሪና በጡት መያዣ፥ በባዶ እግር ነበር የሚደነሰው።ታዲያ ይህ ጉዳይ ሕብረተሰቡን አስቆጥቶት ነበር።ፈረንሳዊቷ ወደ ሀገሯ ስትገባ ንብረቷን ለኔ አስረከበችኝ።ከዚያም አሁን የሞዳኖቫ ሱቅ ከተሠራበት የራስ ኃይሉ ንብረት ላይ ይገኝ የነበረ ቤት በከፍተኛ ገንዘብ ተከራየሁ። ችግሬ ግን የሠለጠኑ ሴቶች ማግኘቱ ነበር።እንዳሁኑ ሴቶች እኔው መርጬ አሠለጠንኳቸው።የፀጉር አሠራሩንም፥ ዳንሱንም አሠለጥንኳቸው።በዚያን ጊዜ ዳንሱም አለባበሱም ብርቅ ስለነበረ ገበያው ደራ።የዚያን ጊዜው ደንበኞቼ ሁሉ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ደርሰዋል።ተጫዋቾቼም ጥሩ ቦታ ላይ ነው ያሉት።ግማሾቹ ትልልቅ ቡና ቤት ከፍተዋል። ሌሎቹ ደግሞ ባለቪላ ሆነዋል።ይህንን መቼም ሁሉ ያውቀዋል። ለጉራና ራሴን ከፍ ለማድረግ አይደለም፣እነሱም አልፎ አልፎ ይጠይቁኛል።እኔ ሳላሰልጥናቸው በፊት በየጣሰው ቤት ክራራቸውን ይዘው ኩር ኩር ያደርጉ ነበር።ያኔ ከሰል ተራ ወይም ቺንኮ ተራ ይሉታል።ቺንኮ የሚሉት ጣሊያኗች ነበሩ።ስሙኒ ማለት ነው።እኛም ወዲያም ወዲህ ብሎ ይበላል ቆንቂቲ አድባሯም ጥሩ ቢያፈራንም ኬቲ እያልን ስለ ከሰል ተራ እንጫወት ነበር።ታዲያ እኔም ሴቶቹ አሳዘኑኝና “ምን ትሠራላችሁ? ቆንጆ ናችሁ፥ታምራላችሁ።ኑ እኔ ጋ ዳንሱን ተማሩ።እኔ ቤት ስንቱ እንግሊዝ፥ ስንቱ አሜሪካ፥ ስንቱ መኳንንት ይመጣል።እኔ ልውሰዳችሁ።”ስላቸው “እኛ ልብስ የለንም። አንቺ ጋ መጥተን ምን እንፈጥራለን?” ሲሉኝ “ግድ የለም።የኔ ጌጥ የኔ ልብስ አለ።” እያልኩኝ እወስዳቸው ነበር።እዚያው ፀጉራቸውን እየተኮስኩ፥ ኩሉን እየኳልኩ አሳመርኳቸው።ዳንሱንም በደንብ አስተማርኳቸው።
ወይዘሮ ሜሪ ያለፈውን ጊዜ በማስታወስ “ይኸውላችሁ እነሱኑ ለማሠልጠን ስል የፀጉር መተኮሻውን ካስክ (ቆብ) እራሴ ላይ እያደረግሁ በሽተኛ ሆንኩ።” አለች።ቀጠል አድርጋ ዘወትር ቅዳሜና እሁድ የኔን ቤት ያየ ግራ ይገባዋል።የሰው ብዛት ይህ ነው አይባልም።ረብሻ እንዳይፈጠር ሰባት ዘበኛ ነበረኝ።
የዳንሱም አይነት የበዛ ነው፤ ታንጐ፤ ቫልስ፥ ቤርዲሉና፥ ማዙካ፥ ቲፕታፕ፥ እነዚህን ሁሉ እንጫወት ነበር።ቤርዲሉና የተባለው ዳንስ ወንድና ሴት እቅፍቅፍ ብለው ፍቅራቸውን የሚወጡቡት ነው።ዳንሱም የሚመራው በአረንጓዴ መብራትና በለስለሳ ሙዚቃ ነው።ማዙካ በውርርድ የሚጫወቱት ዳንስ ነው።ለመጀመሪያ ጊዜ ቀይ መብራት እሥራ ላይ ያዋልኩ ነኝ።እቤቴ ውስጥ የነበረው የመብራት አይነት ብዙ ነበር።ሁሉም ከየአቅጣጫው ፏ ብሎ ይበራል።የውጭ አገር ዜጐችማ ልክ የአገራቸውን እየመሰላቸው ይደነቁ ነበር።

በኅላም ይህ ነገር በጣም እየተለመደ በመሄዱ አንዳንድ ሰዎች ተጋሩኝ። ማዘጋጃ ቤትም ፈፅሞ በውስጥ ሱሪና በጡት መያዣ ብቻ እንዳይደነስ ጥብቅ ትዕዛዝ አወጣ።ስለዚህም ረዥም ልብስ፥ ከላይ ክፍት የሆነ ብቻ ይለበስ ጀመር።ይህ በመጠኑም ቢሆን ገበያዬን ቀንሶብኛል።
እያደር ብዙ ሰዎች ቡና ቤትና ዳንስ ቤት ከፈቱ።ረብሻውም እየበረከተ ሄደ።ከተማው ውስጥ ድብድብ ሆነ።ስሞታውም በዛብኝ።ትኰራለች፥ሰው ትጠየፋለች እያለ ጐረምሳው ይዝትብኝ ጀመር።እኔም ልክ እንደሙሽራ እደበቅ ነበር።ይህቺ ሜሪ የሚሏት የቷ ናት እያለ ሁሉም ይወራረዳል።እኔ የምደበቅበት ምክንያቱ እኔን ለማየት ብቻ ገንዘባቸውን እየከፈሉ የሚመጡ ሰዎች ስለነበሩ ነው።መንግስት ሳይሾመኝ ልክ እንድ አንድ ሚኒስተር በአራዳ ውስጥ አዝ ነበር።
ቅድም እንደተናርኩት እያደር ንትርኩ ጠቡ በመብዛቱ ትንሽ ተበሳጨሁ።ይህንንም ሥራ ለማቆም ወሰንኩ።ሠራተኞቼም እራሳቻችንን እንቻል ስላሉኝ ዳንስ ቤቱን ዘጋሁ።
(ይቀጥላል)
The post “ያን ጊዜ በውስጥ ሱሪና በጡት መያዣ፥ በባዶ እግር ነበር የሚደነሰው።”ሜሪ አርምዴ appeared first on Ethiopia Observer.